Welcome
Login / Register

ከአክሰስ ሪል እስቴት ጋር በተያያዘ የተፈጠረውን ችግር መንግስት እርምጃ መውሰድ ጀመረ

ከአክሰስ ሪል እስቴት ጋር በተያያዘ የተፈጠረውን ችግር መንግስት እርምጃ መውሰድ ጀመረ

ጥር 03 ፣2008

ከ5 አመታት በላይ ከአክሰስ ሪል እስቴት አክሲዮን ማህበር ጋር በተያያዘ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት ከፌደራል መንግስት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች የተካተቱበት ኮሚቴ ተዋቅሮ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ላይ መሆኑንን አስታወቀ፡፡

በሀገሪቱ በተለያዩ መስኮች በርካታ ሪል ስቴቶች መኖራቸውን የገለፁት የኮሚቴው ሰብሳቢና የከተማ ልማትና ቤቶች ሚንስትሩ አቶ መኩሪያ ሀይሌ ከአክስዮኖች ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት በአክሰስ ሪልስቴት ከተፈጠረው ችግር ትምህርት መቀሰሙን ነው የገለፁት፡፡

 

 

አክሰስ ሪል እስቴት በ2002 ዓ.ም ቤቶችን ሰርቶ ለማስረከብ 2500 ከሚሆኑ በውጭ ሀገርና በኢትዮጵያ ከሚኖሩ ቤት ፈላጊዎች 1.4 ቢሊዮን ብር ሰብስቦ ነበር ወደ  ስራ  የገባው፡፡

ይሁንና ሪል ስቴት አልሚው አክሲዮን ማህበር  በገባው ቃል መሰረት ቤቶቹን ገንብቶ ለባለቤቶቹ ሳያስተላልፍ በጊዜው የአክሰስ ሪል ስቴት አክሲዮን ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅና የማህበሩ ሊቀመንበር የነበሩት አቶ ኤልያስ ጠቅል አመልጋ ከሀገር በመውጣታቸው ነበር ችግሩ  የተፈጠረው፡፡

ለችግሩ እልባት ለመስጠትም ከተለያዩ የመንግስት ሚንስቴር መስሪያ ቤቶችና ተቋማት የተውጣጣ ኮሚቴን በማዋቀር አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲመጡ የማድረግና ሌሎች የተለያዩ የመፍትሄ ሃሳቦችን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡

ይሁንና ችግሩ በሚፈለገው ፍጥነት አለመፈታቱን ከአክሰስ ሪልስቴት ቤት ለመግዛት የተዋዋሉ ግለሰቦች ገልፀዋል፡፡

መንግስት ችግሩን ለመቅረፍ በርካታ የመፍትሄ ስራዎችን ማከናወኑንና ጉዳዩ ውስብስብ በመሆኑ ጊዜ መውሰዱን ነው የፍትህ ሚንስትሩ አቶ ጌታቸው አምባዬና የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል አሰፋ አብዩ የተናገሩት፡፡

ይሁንእንጂ ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ የሚያስችሉ ዋና ዋና የመፍትሄ አቅጣጫዎች መቀመጣቸውን የከተማ ልማትና ቤቶች ሚንስትሩ አቶ መኩሪያ ሀይሌ ገልፀዋል፡፡

የአክሰስ ሪልስቴት መስራችና የቀድሞ የቦርድ ሊቀመንበር የነበሩት አቶ ኤርሚያስ አመልጋ በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑን ከፌደራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡

ሪፖርተር፡- ሀብታሙ ድረስ

Related Articles

Post your comment

Comments

Be the first to comment