Welcome
Login / Register

‹‹ፍቅር እንደገና፤እንደ ዱሮው እንዋደድ›› ኢሳያስ አፈወርቂ

‹‹ፍቅር እንደገና፤ እንደ ዱሮው እንዋደድ›› ኢሳያስ አፈወርቂ | በኃይሉ ሚዴቅሳ ከአራት ኪሎ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 19፣ 2010 (ድሬቲዩብ) ሰሞኑን የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ረጃጅምና አሰልቺ መግለጫዎችን ሲሰጡ ሰንብተዋል፡፡ በመግለጫቸው መጸጸት፣ እብሪት፣ ጀብደኝነት፣ እልህ ይነበብ ነበር፡፡ ፕሬዚዳንቱ ከተጸጸቱባቸው ጉዳዮች አንዱ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸው ግንኙነት ነው፡፡

 

አቶ ኢሳያስ እንዳሉት ያለፉት 25 ዓመታት ለሁለቱ ሃገራት ግንኙነት አክሳሪ ነበር፡፡ በእሳቸው አገላለጽ ባለፉት 25 ዓመታት የኤርትራ ሕዝብና መንግሥት ከስሯል፤ ከኢትዮጵያ ጋር ተጣልቶ ያተረፈው ነገር የለም፡፡ እናም ለዚህ መፍትሔ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ መፍትሔው ግንኙነቱን ከ1990ው ጦርነት በፊት ወደነበረው መመለስ የሚል ሆኗል፤ በአቶ ኢሳያስ አገላለጽ፡፡

ይሄ ነው የአቶ ኢሳያስ ጀብደኛነት፡፡ የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነት ከ1983-1990 ዓ.ም እንደነበረው ይሁን ማለት፣ አሁንም ሻዕቢያ ዘራፊ ይሁን፤ አሁንም ኤርትራዊያን ሕገ-ወጥ ንግዶችንና ቢዝነሶችን በኢትዮጵያ ይከዉኑ፤ ዘንድሮም እንደ ያኔው ሻዕቢያ የዓይናቸው ቀለም አላማረኝም ያላቸውን ኢትዮጵያዊያን ያፍን የሚል ነው፡፡ በአጭር አገላለጽ ኢ-ፍትሀዊውና ለኤርትራ ያደላው የሁለቱ ሃገራት ግንኙነት ወደነበረበት ይመለስ የሚል ነው፡፡

ተደጋግሞ እንደተገለጸው ከመቶ ዓመታት በላይ ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ችግር እንደ አንድ ዋነኛ መንስኤ የምትጠቀሰው ምድር ኤርትራ ነች፡፡ መቼም ግን በነዚያ ሰባት ዓመት እንዳደረገችን አድርጋን አታውቅም፡፡ ከ1983-1990 ዓ.ም የነበረው ጊዜ ማለት፣ አንድ የቡና ዛፍ እንኳ የሌላት ኤርትራ ከኢትዮጵያ ዘርፋና በብር በርካሽ ገዝታ ከአፍሪካ አንደኛ ቡና ኤክስፖርተር የሆነችበት፣ ኤርትራዊያን በኢትዮጵያ ያለገደብ የነገዱበት፣ ሰሊጥና ጥጥ ሳይቀር ላኪ የሆኑበት፣ የኤርትራ ሸቀጥ ያለምንም ታሪፍና ቀረጥ በኢትዮጵያ ገበያዎች ላይ የተራገፈበት፣ የኤርትራ ፋብሪካዎች በዝርፊያና በማጭበርበር ከኢትዮጵያ ጥሬ እቃዎችን የወሰዱበት ነው፡፡

ኢትዮጵያዊያን በአንጻሩ በኤርትራም በኢትዮጵያም በሻዕቢያ የታፈኑበት፣የታሰሩበትና የተገደሉበት፣ በኤርትራ መነገድ ተከልክለው ሐድጊ (አሕያ) እየተባሉ በሬዲዮና ቴሌቭዥን የተሰደቡበት፣ የሻዕቢያ የደኅንነት መዋቅር ኢትዮጵያዊያንን በየትኛውም የንግድ መስክ ስኬታማ እንዳይሆኑ ያዋከበበት፣ እነ አቶ ኢሳያስ ጥሬ ሥጋ ሳይቀር ከአዲስ አበባ ያጓጉዙበት ነው- ያ ከ1990 ዓ.ም በፊት የነበረው ግንኙነት፡፡

ይህንን ነው እንግዲህ አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ መመለስ አለበት የሚሉት ግንኙነት፡፡ ያንን ኢፍትሐዊ ግንኙነት የሚናፍቅና የሚፈቅድ ኢትዮጵያዊ ካለ ሌላ ጦርነት ሌላ አበሳ አምሮታል ማለት ነው፡፡

እንደሚታወቀው ኤርትራዊያን የወረሩንና በ10ሺሕዎች የሚቆጠሩ የድሃ ልጆችን እንድገብር ያደረጉን፣ በኢትዮጵያ የሚያካሂዱት ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ገደብ ይበጅለት ስለተባለ ነው፡፡ አቶ ኢሳያስ ገደብ ከተበጀ ደግሞ ኢኮኖሚያቸው ያለ-ኢትዮጵያ ተስፋ እንደሌለው ገባቸውና ኢትዮጵያ ላይ ጦር አዘመቱ፡፡ አሁን ደግሞ ‹‹ከጦርነቱ በፊት የነበረው ግንኙነት መልካም ነበር እርሱን መመለስ አለበት›› አሉ፡፡ ይህ አሁንም ዘራፊ፣ አፋኝና በጥባጭ ሆኜ ኢትዮጵያ ውስጥ ልግባ የሚል ነው፡፡

አቶ ኢሳያስ ቢገባቸው እንኳንም ከ1983-1990 ዓ.ም ያለው ግንኙነት ቀርቶ ከ1983 ዓ.ም በፊትም የነበረው የኢትዮጵያና ኤርትራ ሁኔታ ኢትዮጵያን የጎዳና ያገለለ ነበር፡፡ ለምሳሌ በ1952ዓ.ም በ14ቱም ጠቅላይ ግዛቶች የነበረው የኢንዱስትሪ ካፒታል 44 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ ከዚህ ውስጥ የኤርትራ ብቻ 16 ሚሊዮን ነበር፡፡ በ1969ዓ.ም በ12 ጠቅላይ ግዛቶች የተመደበው በጀት፣188 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ከዚህ ውስጥ ኤርትራ ብቻ 153.6 ሚሊዮን ብር ተበጅቶላታል፡፡

በትምህርትም እንደዚያው ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ውስጥ 20 በመቶዎቹ ኤርትራዊያን ነበሩ፡፡ በዩኒቨርሲቲ ትምኅርትም 25 በመቶ የሚሆኑት ኤርትራዊያን ነበሩ፡፡ይህን ሁሉ ጥቅም ያገኙት ኢትዮጵያዊያን እየተጎዱና መሃይም እየሆኑ ነው፡፡

ጣሊያንማ ኤርትራዊያንን አስመራን ሲገነባ የጉልበት ሰራተኛና የገራዥ ጠጋኝ ከማድረግ የዘለለ ትምኅርት እንዳላሰለጠናቸው እነርሱም አይክዱም፡፡

እና ምን ለማለት ነው፤ እንኳንም በሻዕቢያና በኢሕአዴግ ዘመን ያለው የሁለቱ ሃገራት ግንኙነት ቀርቶ ከዚያም በፊት አንድ አገር በነበሩ ጊዜ የነበረው ሁኔታ ኤርትራን ጌታ ፣ኢትዮጵያን ሎሌ ያደረገ ነበር፡፡ ሁለቱም ግንኙነቶች (ከ1983 በፊትም ሆነ በኋላ ያሉት) ለእኛ የሚጠቅሙን ስላልነበሩ ምሳሌ ሊሆኑ አይችሉም፡፡

እናም ለአቶ ኢሳያስ፣‹‹ተመልሼ ልምጣ ማለትዎን የምንቀበለው እርስዎና ሕዝብዎ ዓለማቀፍ ሕጎችን ካከበሩ ነው›› የሚል መልዕክት መላክ ያስፈልገናል፡፡እንኳን መንግሥት መጥቶብን ስደተኞቻቸውም ኑሮ አስወድደውብናል!!    source: diretube

 

 

Related Articles

Post your comment

Comments

Be the first to comment